"የእግዚአብሔር ፍቅር እና ፍትሕ" 1ኛ ትምህርት "እግዚአብሔር እንዲሁ ይወዳል::"
SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ
የእግዚአብሔር ፍቅር እና ፍትሕ
1ኛ ሩብ ዓመት 2025
ጥር፣ የካቲት፣ መጋቢት 2017 ዓ.ም.
መደበኛ እትም
1ኛ ሩብ ዓመት
ከታህሳስ 19 - መጋቢት 19/2017 ዓ.ም
1 ዮሐ. 4:8 እና 16 እግዚአብሔር ፍቅር ነው ይላል። መላው መጽሐፍ ቅዱስ ይህን እውነታ ይመሰክራል። የክርስትና እምነት ማዕከሉ የእግዚአብሔር ፍቅር ነው። ፍቅር የእግዚአብሔር ማንነት እምብርት ነው፤ እኛም የምናምነውና የምንሰራው ነገር ሁሉ ማዕከል ፍቅር መሆን አለበት። በዚህ መሠረት ፍቅርን የምንረዳበት መንገድ በእምነታችን እና በድርጊታችን ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል።
ለምሳሌ አንድ ሰው የእግዚአብሔር ፍቅር በሥራ ይገኛል ብሎ ካመነ፣ ኃጢአተኛና ያልበቃ ስለሆነ እግዚአብሔር እንደማይወደው ሊያስብ ይችላል። ከሌሎችም ጋር ባለው ግንኙነት፣ ሰዎችን ይወዳቸው ዘንድ፣ እነርሱ አስቀድመው መልካም ነገር ማድረግ ይኖረባቸዋል ብሎ ያስባል፡- ይህም ለውድቀት መንስኤ ይሆናል።
ስለዚህ የእግዚአብሔርን ፍቅር የምንረዳበት መንገድ በእምነታችን እና በልምምዳችን ላይ ትልቅ አንድምታ አለው። ለመሆኑ ፍቅር ምንድን ነው? ፍቅርን እንዲገልጹ አሥር ሰዎችን ቢጠይቋቸው፣ አሥር የተለያዩ ምላሾችን ሊያገኙ ይችላሉ። በክርስቲያኖች መካከል እንኳን፣ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብዙ አፈ-ታሪኮች እና የተሳሳቱ መረዳቶች አሉ።
ለምሳሌ ክርስቲያኖች ለሚቀጥሉት ጥያቄዎች የተለያዩ ምላሾችን ይሰጣሉ፡ - የእግዚአብሔር ፍቅር መስጠት ብቻ እንጂ ምላሽ አይጠብቅምን? መለኮታዊው ፍቅር ራሱን መስዋዕት የሚያደርግ ብቻ ነው ወይስ እግዚአብሔር በሰዎች ሐሴት ሊያደርግ ይችላል? የእግዚአብሔር ፍቅር ስሜታዊ ነው? በእርግጥ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይጠነቀቃል? የእግዚአብሔር ፍቅር ቸል ሊባል ወይም ሊገፋ ይችላል? እግዚአብሔር ከፍጡራን ጋር የሰጥቶ መቀበል የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ይገባል? ቁጣ ከፍቅር ጋር አይጣጣምም? ፍቅር እና ፍትሕ እንዴት አብረው ይኖራሉ? እግዚአብሔር ፍቅር ከሆነ፣ ክፋት በዚህ ዓለም ላይ ለምን እጅግ በዛ? ሰዎች እንደ እግዚአብሔር ሊወዱ ይችላሉ? ከሆነ ያ ምን ሊመስል ይችላል?
ከላይ ለተጠቀሱት ለአንዳንዶቹ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልሶች ግልጽ ሊመስሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን ክርስቲያኖች ለመለኮታዊው ፍቅር ያላቸውን አመለካከት አስመልክቶ ብዙ ጊዜ ክርክሮች ይነሳሉ። ግልጽ የሚመስሉ ብዙ ምላሾች በጥልቀት ስንመረምራቸው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ከሚያስተምረው ጋር የማይጣጣሙ ሆነው ይገኛሉ።
እነዚህን ጥያቄዎች ሁሉ በአንድ ጊዜ አንፈታቸውም፤ ነገር ግን እነዚህን እና ሌሎች ጥያቄዎችን በዚህ ሩብ አመት እንዳስሳለን። በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅር ከምናስበው በላይ እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን እናያለን። በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተገለጸው የእግዚአብሔር ፍቅር፣ በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን "ስለ ፍቅር" ከሚነገሩ ሃሳቦች እጅግ የላቀ ነው። በሚቀጥሉት ሳምንታት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር የተገለጹትን አንኳር እና ውብ ገጽታዎች በጥልቀት እንመለከታለን።
ጥናታችንን ስንቀጥልም መለኮታዊው ፍቅር እና ፍትሕ እንዳይነጣጠሉ ሆነው የተጋመዱ መሆናቸውን እናያለን። በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጸው እግዚአብሔር ፍትሕን ይወዳል (ለምሳሌ፡- ኢሳ. 61፡8ን ይመልከቱ)። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጠው፣ መለኮታዊው ፍቅር እና ፍትሕ ስለማይነጣጠሉ፣ አንዱ ከሌላው ውጭ ሊኖር አይችልም። እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ፣ በዚህ ዓለም ያለው ኢ-ፍትሃዊነትና ስቃይ እጅግ ያሳስበዋል፤ ራሱንም ከተጨቆኑና ከተሰቃዩት ጋር አንድ አድርጎ በመቁጠር፣ ክፋት በፍጥረት ላይ ባመጣው ስቃይና ሀዘን ውስጥ በፈቃዱ ራሱን ሰጠ—ራሱ ከሁሉም በላይ ተሰቃየ። ስለዚህም እግዚአብሔር ራሱ ከሁሉ ይልቅ የክፋት ተጠቂ ሆነ።
እግዚአብሔር እያንዳንዱን ሰው ከምንገምተው በላይ ስለሚወድ፣ በክፋት እና በስቃይ በተደጋጋሚ ማዘኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን።
የእግዚአብሔርን ጥልቅ ፍቅር፣ ክርስቶስ በሕዝቡ ላይ፡- “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፣ ዶሮ ጫጩቶቿን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም” እያለ በተናገረው እንጉርጉሮ ውስጥ ማየት ይቻላል (ማቴ. 23፡37)።
ፍቅር የሆነው የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ፣ ያ ፍቅር ችላ ስለተባለና ስለተገፋ ልቡ እንደተሰበረና እንዳዘነ በቃሉ ውስጥ ተገልጧል። ቃሉ እግዚአብሔር ፍቅሩን በዓለማት ሁሉ ለማስፈን ስላደረገውና እያደረገ ስላለው ነገር ይተርካል። ይህ የዚህ ሩብ ዓመት ትምህርት ርዕስ ነው።
ጆን ሲ. ፔካም የአድቬንቲስት ሪቪው ተባባሪ አርታኢ ናቸው። ይህ የጥናት መመሪያ በተጻፈበት ጊዜ፣ እሳቸው በአንድርውዝ ዩኒቨርሲቲ በሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ስነመለኮት ሴሚነሪ የነገረ መለኮት እና የክርስቲያን ፍልስፍና ፕሮፌሰር ነበሩ።
SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )
ታህሣሥ 19 - 25
1ኛ ትምህርት
Dec 28 - Jan 3
እግዚአብሔር እንዲሁ ይወዳል::
ሰንበት ከሰዓት በኋላ
ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ዘጸ. 33:15–22፤ ሆሴዕ 14:1-4፤ ራእይ 4:11፤ ዮሐንስ 17:24፤ ማቴ. 22:1–14፤ ዮሐንስ 10:17፣ 18
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ቁጣዬ ከእርሱ ዘንድ ተመልሶአልና ዓመፃቸውን እፈውሳለሁ፣ በገዛ ፈቃዴ እወድዳቸዋለሁ” (ሆሴዕ 14፡4)።
ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ጴጥሮስ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ቢክደውም፣ (ማቴ. 26፡34) ክህደቶቹ ግን የታሪኩ መጨረሻ አልነበሩም። ከትንሣኤ በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን “ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ግልገሎቼን አሰማራ አለው። ደግሞ ሁለተኛ፡- የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሦስተኛ ጊዜ፡- የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። ሦስተኛ ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና፡- ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም፡ - በጎቼን አሰማራ አለው” (ዮሐንስ 21፡15–17)። ጴጥሮስ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ እንደካደው ሁሉ፣ ኢየሱስም “ትወደኛለህን?” በሚለው ወሳኝ ጥያቄ አማካኝነት ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ የራሱ አድርጎታል። ምንም እንኳን እኛ ያለንበት ሁኔታ ከጴጥሮስ የተለየ ቢሆንም፣ መርሆው ግን በብዙ መልኩ ተመሳሳይ ነው። ኢየሱስ ጴጥሮስን የጠየቀውን ጥያቄ፣ እግዚአብሔር በእኛ ዘመንና በምንኖርበት ቦታ ለእያንዳንዳችን የሚያቀርበው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡ - ትወደኛለህን?
ሁሉም ነገር ለዚህ ጥያቄ በምንሰጠው ምላሽ ላይ የተመረኮዘ ነው።
SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )]
እሑድ ታህሣሥ 20 Dec 29
ከምንገምተው በላይ
እግዚአብሔር እኛን "ትወደኛለህን" ብሎ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር ራሱ እያንዳንዱን ሰው እንዲሁ ይወዳል። በእርግጥ እርሱ ልትገምተው ከምትችለው በላይ አንተን እንዲሁ ይወድሃል። ይህንን ፍቅር በዘመናት ሁሉ ለሕዝቡ ባደረገው ድርጊት እናውቃለን።
ዘጸ. 33፡15–22ን ያንብቡና የጥቅሶቹን አውድ እና የተገለጹበትን ሁኔታ ያስቡ። ይህ ክፍል በተለይም ቁጥር 19 ስለ እግዚአብሔር ፈቃድና ፍቅር ምን ይገልጻል?
ሁሉም ነገር ያበቃለት ይመስል ነበር። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከግብፅ ባርነት በድንቅ ሁኔታ ነፃ ካወጣ በኋላ፣ ብዙም ሳይቆይ እሥራኤላውያን በእግዚአብሔር ላይ ዓምፀው የወርቅ ጥጃ አመለኩ። ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ፣ ያደረጉትን አየና አሥርቱን ትእዛዛት የያዙትን ጽላቶች ጥሎ ሰበራቸው። ምንም እንኳን ሕዝቡ እግዚአብሔር እንዲሁ የሰጣቸውን የቃል ኪዳኑን ዕድሎች እና በረከቶች የማግኘት መብታቸውን ቢያጡም፣ ምንም እንኳን የኪዳኑ በረከቶች የማይገባቸው ቢሆንም፣ እግዚአብሔር በኪዳኑ ከእነርሱ ጋር ለመቀጠል እንዲሁ መረጠ።
በዘፀአት 33፡19 ላይ፡- “ይቅር የምለውን ይቅር እላለሁ፣ የምምረውንም እምራለሁ” የሚለው ቃል ብዙ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ እግዚአብሔር በዘፈቀደ ለአንዳንዶች ሩኅሩኅና መሃሪ፣ ለሌሎች ግን እንዳልሆነ ተደርጎ ይስተዋላል። ነገር ግን እንደ አውዱ ከሆነ፣ እግዚአብሔር አንዳንዶችን ይቅር ብሎ እንደሚምር እና ሌሎችን ግን ችላ እንደሚል እየተናገረ አይደለም። እግዚአብሔርም የሚሠራው በዚህ መልኩ አይደለም፤ እንዲያውም እግዚአብሔር አንዳንዶቹን እንዲጠፉና ለዘለዓለም እንዲኮነኑ አስቀድሞ ወስኗል የሚለውን የተሳሳተ ግን በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን የሥነ-መለኮት አስተምሮ ይቃወማል። እግዚአብሔር እንዲሁ ይወዳል
ታዲያ እግዚአብሔር እዚህ ላይ ምን እያለ ነው? እግዚአብሔር የሁሉ ፈጣሪ ስለሆነ፣ ለማይገባቸው ሰዎች እንኳን ፣ ጸጋን እና ርኅራኄን እንዲሁ የመስጠት መብትና ሥልጣን እንዳለው እያወጀ ነው። የወርቅ ጥጃ በማምለክ ቢያምፁም፣ ምንም እንኳን የማይገባቸው ቢሆኑም፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ለሕዝቡ ለእሥራኤል መሃሪ መሆኑን ያሳያል።
ይህ እግዚአብሔር ፍቅሩን ከምንገምተው በላይ ከገለፀባቸው ከብዙ አጋጣሚዎች አንዱ ነው። ለሁላችንም መልካም ዜና አይደል? እግዚአብሔር ለአንተ ከምትገምተው በላይ ፍቅሩን አየገለጸ ያለው በምን በምን መንገዶች ነው?
SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )
ሰኞ ታህሣሥ 21 Dec 30
ምላሽ የተነፈገው ፍቅር
እግዚአብሔር ለወደቀው የሰው ዘር ያለውን አስገራሚ ፍቅር በሆሴዕ ታሪክ ውስጥ እናገኛለን። እግዚአብሔር ነቢዩን ሆሴዕን እንዲህ ብሎ አዘዘው፡- “ምድሪቱ ከእግዚአብሔር ርቃ ታላቅ ግልሙትና ታደርጋለችና ሂድ፤ ጋለሞታን ሴትና የግልሙትናን ልጆች ለአንተ ውሰድ አለው” (ሆሴ. 1፡2):: ሆሴዕ እና ታማኝ ያልሆነችው ሚስቱ፣ እግዚአብሔር ታማኝ ላልሆኑትና በመንፈሳዊ ግልሙትና ለተዘፈቁት እሥራኤላውያን ያለውን ፍቅር የሚያሳዩ ሕያው ምስክሮች መሆን ነበረባቸው። ይህም ለማይገባቸው ሰዎች እንዲሁ የተበረከተው የእግዚአብሔር ፍቅር ታሪክ ነው።
እግዚአብሔር ታማኝ እና አፍቃሪ ቢሆንም፣ ሕዝቡ በእርሱ ላይ ደግመው ደጋግመው አመፁበት። ስለዚህ ቃሉ እግዚአብሔርን፣ በተደጋጋሚ ታማኝ ያልሆነችውን የባለቤቱን ፍቅር ምላሽ የማይጠብቅ አፍቃሪ አድርጎ ይመስለዋል። እርሱ ሕዝቡን በፍፁም ታማኝነት ወደዳቸው፤ እነርሱ ግን ንቀውት ሌሎች አማልክትን በማገልገልና በማምለክ እጅግ አሳዘኑት፤ ሊጠገን የማይችል እስኪመስል ድረስ ኪዳኑን አፈረሱ።
ሆሴዕ 14:1–4ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስላለው ጽኑ ፍቅር ምን ይገልፃሉ?
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
ሕዝቡ በተደጋጋሚ ካመፁም በኋላ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- “ዓመፃቸውን እፈውሳለሁ፣ በገዛ ፈቃዴም እወድዳቸዋለሁ።” “በገዛ ፈቃዴም እወድዳቸዋለሁ” በሚለው ሐረግ ውስጥ የሚገኘው “በፈቃዴ” የሚለው ቃል የተተረጎመው ነዳባ ከሚባለው የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን በፈቃደኝነት የተለገሰን ነገር ያመለክታል። በመቅደስ አገልግሎት ውስጥ በገዛ ፈቃድ የሚሰጥ ስጦታን ለመግለፅ ጥቅም ላይ የዋለው ተመሳሳይ ቃል ነው።
በሆሴዕ እና በሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች፣ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው አስደናቂ ታማኝነትና ርኅራኄ ይታያል። ምንም እንኳን ደጋግመው ሌሎች አፍቃሪዎችን ቢከተሉም፣ ሊጠገን የማይችል እስኪመስል ድረስ የቃል ኪዳኑን ግንኙነት ቢያፈርሱም፣ እግዚአብሔር በገዛ ፈቃዱ ፍቅሩን በነሱ ላይ ማፍሰሱን ቀጠለ። ሕዝቡ የእግዚአብሔር ፍቅር አይገባቸውም ነበር፤ እንዲያውም ፍቅሩን ንቀውት መብታቸውን አጥተው ነበር። ቢሆንም እግዚአብሔር ማንም ሳያስገድደው ፍቅሩን መለገሱን ቀጠለ። ቃሉ የእግዚአብሔርን ፍቅር ነፃ እና በፈቃዱ የሚሰጥ መሆኑን ያሳያል።
ብዙ ሰዎች እግዚአብሔርን ሩቅ፣ ጨካኝ ገዥ እና ዳኛ አድርገው ያስቡታል። እግዚአብሔር ታማኝ ባልሆነች ባለቤቱ ምላሽ እንደተነፈገው አፍቃሪ በመሆኑ የተናቀና የሚያዝን እንደሆነ መመሰሉ እግዚአብሔርን በተለየ መንገድ እንዲያዩት የሚረዳዎ እንዴት ነው? ከአምላክ ጋር ያለዎትን ግንኙነት የሚያዩበትን መንገድ እንዴት ይለውጠዋል?
SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )
ማክሰኞ ታህሣሥ 22 Dec 31
በነጻ የተሰጠ ፍቅር
እግዚአብሔር ፍቅሩን ያለማቋረጥ እንዲሁ የለገሰው በተደጋጋሚ ለሚያምፀው ለእሥራኤል ብቻ ሳይሆን፣ ለእኛም ገና ኃጢአተኞች ሳለን እንዲሁ በነፃ ፍቅሩን መስጠቱን ቀጥሏል። የእግዚአብሔር ፍቅር በጭራሽ አይገባንም፤ በሥራም ልናገኘው አንችልም። እግዚአብሔር ከኛ ምንም አይፈልግም (ሐዋ. 17፡ 25)። እግዚአብሔር ለኛ ያለው ፍቅር በራሱ በጎ ፈቃድ የተመሰረተ ነው። እግዚአብሔር እንዲሁ ይወዳል ራእይ 4:11ን ከመዝሙር 33:6 ጋር ያነፃፅሩ። እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር ፍጥረትን እንደፈለገው ስለ መፍጠሩ ምን ይነግሩናል?
እግዚአብሔር ይህንን ዓለም በፈቃዱ ፈጠረው። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ክብር፣ ውዳሴና ኃይል ሁሉ ይገባዋል። እግዚአብሔር የትኛውንም ዓለም መፍጠር አያስፈልገውም ነበር። ዓለም ገና ሳይፈጠር፣ እግዚአብሔር በሥላሴ (በመለኮት) መካከል በነበረው የፍቅር ግንኙነት ይደሰት ነበር።
ዮሐንስ 17:24ን ያንብቡ። ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ስለነበረው የእግዚአብሔር ፍቅር ምን ይነግረናል?
እግዚአብሔር ለፍቅሩ መገለጫ ፍጡራን አያስፈልጉትም ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ባሕርይው ፍቅር ስለሆነ፣ እግዚአብሔር ዓለምን ለመፍጠር እና ከፍጡራን ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዲኖረው መረጠ።
እግዚአብሔር ይህን ዓለም በፈቃዱ የፈጠረው ፍቅሩን አብዝቶ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎች በኤደን በኃጢአት ከወደቁ በኋላም ሆነ በግል ኃጢአት ከሠራን በኋላም እግዚአብሔር ሰዎችን እንዲሁ በነፃ መውደዱን ቀጥሏል።
አዳምና ሔዋን በኤደን ከወደቁ በኋላ፣ በሕይወት መኖር እና የእግዚአብሔርን ፍቅር የመቀበል መብት አልነበራቸውም። ነገር ግን "ሁሉን በስልጣኑ ቃል" የሚደግፈው እግዚአብሔር (ዕብ. 1:3)፣ ከታላቅ ፍቅሩ፣ ምህረቱና ጸጋው የተነሳ በሕይወት እንዲኖሩና የሰው ዘርም ከራሱ ጋር የሚታረቅበትን መንገድ አዘጋጀ። ያ እርቅ እኛንም ያካትታል።
አለማችን የወደቀና ክፉ ቢሆንም፣ እግዚአብሔር ፍቅሩን መለገስ መቀጠሉ ስለ ፍቅሩና ባሕርይው ምን ይነግረናል? ይህ እውነት በምላሹ እሱን እንድንወደው ሊያደርገን የሚገባው እንዴት ነው?
SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )
ረቡዕ ታህሣሥ 23 Jan 1
የተጠሩ ብዙዎች፣ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸው
እግዚአብሔር ሰዎችን በገዛ ፈቃዱ ስለሚወዳቸው፣ በምላሹም እንዲወዱት ይጋብዛቸዋል። እግዚአብሔር ለሰዎች ፍቅሩን ለመቀበል ወይም ላላመቀበል የምርጫ ነፃነት እንደሰጣቸው፣ ክርስቶስ ስለ ሠርግ ግብዣ በተናገረው ምሳሌ ላይ በግልጽ ይታያል። ማቴዎስ 22:1-14ን ያንብቡ። የዚህ ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው?
ክርስቶስ ስለ ሰርጉ ግብዣ በተናገረው ምሳሌ ላይ፣ አንድ ንጉሥ ለልጁ ሰርግ አዘጋጅቶ አገልጋዮቹን “ወደ ሰርጉ የታደሙትን እንዲጠሩ” ይልካቸዋል።
ነገር ግን የታደሙት "ሊመጡ አልወደዱም" (ማቴ. 22:2, 3)። ንጉሡ ከአንድ ጊዜ በላይ የታደሙትን እንዲጠሩዋቸው ባሮቹን ላከ፣ እነርሱ ግን ጥሪውን ችላ አሉ፣ ይባስ ብለውም ባሪያዎቹን ይዘው ገደሏቸው (ማቴ. 22፡4-6)።
ንጉሡ አገልጋዮቹን የገደሉትን ከቀጣ በኋላ፣ ሌሎች አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው:- “ሰርጉስ ተዘጋጅቷል፣ ነገር ግን የታደሙት የማይገባቸው ሆኑ፤ እንግዲህ ወደ መንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ” (ማቴ. 22:8, 9)። የሰርግ ልብስ ያልለበሰው ሰው ወደ ውጭ ከተጣለ በኋላ፣ በሰርጉ ግብዣ ለመታደም የሰርግ ልብስ ከንጉሱ መቀበል አስፈላጊ መሆኑን አመልክቶ፣ ምሳሌውን “የተጠሩ ብዙዎች፣ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸው” (ማቴ. 22፡14) የሚለውን ትልቅ ትርጉም ያለውን ሐረግ በመናገር ይቋጨዋል ።
ይህ ምን ማለት ነው? በመጨረሻ “የተመረጡት” የጌታን የሰርግ ግብዣ ጥሪ በፈቃዳቸው የተቀበሉ ናቸው ማለት ነው።
በርግጥ እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው ወደ ሰርጉ ድግስ ይጠራል ። ሆኖም ማናችንም ብንሆን የእግዚአብሔርን ፍቅር እምቢ ልንል እንችላለን። የምርጫ ነፃነት ለፍቅር አስፈላጊ ነው። እግዚአብሔር ፍቅሩን እንድንቀበል ማናችንንም እግዚአብሔር እንዲሁ ይወዳል በፍጹም አያስገድድም። የሚያሳዝነው ግን ከእግዚአብሔር ጋር የፍቅር ግንኙነት እዳይኖረን መቃወም እንችላለን።
“የተመረጡት” ግብዣውን የሚቀበሉ ናቸው። እግዚአብሔርን ለሚወዱት፣ እኛ ልንገምተው ከምንችለው በላይ፣ አስደናቂ ነገሮችን እግዚአብሔር አዘጋጅቷል። ሁሉም የሚንጠለጠለው በፍቅር እና በፍቅር ውስጥ ባለው የምርጫ ነፃነት ላይ ነው። የሰርጉን ግብዣ መቀበልህንና በአግባቡ መልበስህን ሕይወትህ ያሳያል?
SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )
ሐሙስ ታህሣሥ 24 Jan 2
ስለኛ ተሰቀለ
እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው ከእርሱ ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዲኖረው ይጋብዛል፣ ነገር ግን ግብዣውን በፈቃዳቸው የሚቀበሉት ብቻ ዘላለማዊ ደስታን ያገኛሉ። በሠርጉ ግብዣ ምሳሌ እንደታየው፣ ንጉሡ የጠራቸው ብዙዎቹ "ለመምጣት ፈቃደኛ አልነበሩም" (ማቴ. 22: 3)።
ክርስቶስ ከመስቀሉ ጥቂት ቀደም ብሎ እንዲህ ሲል በሀዘን ተናገረ:- “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፣ ዶሮ ጫጩቶቿን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም” (ማቴ. 23፡37)።
ክርስቶስ በጉያው ሊሰበስባቸው ፈለገ፣ እነርሱ ግን ፈቃደኛ አልነበሩም። ቴሎ የሚባለው ተመሳሳይ የግሪክ ግስ ክርስቶስ እነርሱን ለማዳን መፈለጉን እና እነሱ ግን ለመዳን ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ለመግለጽ ጥቅም ላይ ውሏል። ይህ ቃል በማቴ. 22፡3 ላይም ይገኛል።
ሆኖም ክርስቶስ ወደ መስቀል የሄደው ለእነዚህ ሰዎች እና ለእኛ ሲል ነው።
አስደናቂ ፍቅር! በኃጢአት ምክንያት ሰው ሞት የሚገባው ሆኖ ሳለ፣ እግዚአብሔር ራሱ (በክርስቶስ) ዋጋ ከፍሎ በሰማይና በምድር መካከል የተቋረጠውን ግንኙነት ለማደስ መንገድን አዘጋጀ። ምንም እንኳን ከርሱ ነፃ ቁርጠኝነት ውጭ ምንም ግዴታ ባይኖርበትም፣ አሁንም ፍቅሩን በኛ ላይ ማፍሰሱን ቀጥሏል። የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት ዮሐ. 10:17፣ 18ን ያንብቡ። ከገላ. 2:20 ጋር ያስተያዩ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ለእኛ ያለው መልእክት ምንድን ነው?
የእግዚአብሔር ፍቅር በአስደናቂ ሁኔታ በታየበት በመስቀሉ፣ ክርስቶስ በራሱ ፍቃድ ለእኛ ሲል ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ እናያለን። ክርስቶስ ህይወቱን አሳልፎ የሰጠን “በራሱ ተነሳሽነት” ነው። ማንም ሕይወቱን ከእርሱ አልወሰደበትም፣ አለም ሳይፈጠር በፊት በሰማይ በተዘጋጀው የደህንነት እቅድ መሠረት ራሱን በፈቃዱ አቀረበ።
“የእኛ የደህንነት እቅድ ከአዳም ውድቀት በኋላ የተነደፈ አልነበረም።
ይልቅስ ‘ከዘላለም ዘመንም የተሰወረው‘ ምስጢር ተገለጠ (ሮሜ 16፡25)። ከዘመናት በፊት የእግዚአብሔር ዙፋን መሠረት የሆነው መርህ ተዘረጋ። ገና ከጅምሩ እግዚአብሔር እና ክርስቶስ የሰይጣንን ክህደት እና በአታላዩ አማካኝነት የሰው ዘር እንደሚወድቅ ያውቁ ነበር። ኃጢአት እንዲኖር የእግዚአብሔር ፈቃድ አልነበረም፣ ነገር ግን የኃጢአትን መከሰት አስቀድሞ ተመለከተ፣ እናም አስፈሪውን አደጋ ለመቀልበስ ሁኔታዎችን አዘጋጀ። ለዓለማችን የነበረው ፍቅር ታላቅ ስለነበር፣ ‘በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ’ አንድያ ልጁን ለመስጠት ቃል ኪዳን ገባ (ዮሐ. 3፡16)።”—ኤለን ጂ. ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ. 22.
SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )
ዓርብ ታህሣሥ 25 Jan 3
ተጨማሪ ሀሳብ
የክርስቶስ ምሳሌያዊ ትምህርቶች ከሚለው የኤለን ጂ. ኋይት መጽሐፍ “ሙሽራውን ለመገናኘት” የተሰኘውን ርዕስ ከገጽ 405–421 ያንብቡ።
"ዓለምን የሸፈነው እግዚአብሔርን በተሳሳተ መንገድ የመረዳት ጨለማ ነው። ሰዎች ስለ ባሕሪይው ያላቸውን እውቀት እያጡ ነው። ባሕሪይው በተሳሳተ መንገድ ተስተውሏል፣ ተተርጉሟልም። በዚህ ዘመን የሚያበራ እና ተጽእኖና የማዳን ኃይል ያለው የእግዚአብሔር መልእክት ሊታወጅ ይገባል። ባሕሪይውም ሊታወቅ ያስፈልጋል። ወደ ጨለማው ዓለም የክብሩ፣ የመልካምነቱ፣ የምሕረቱ እና የእውነት ብርሃን መብራት ይኖርበታል። እግዚአብሔር እንዲሁ ይወዳል
በነብዩ ኢሳያስ ሊሰራ የታቀደው እንዲህ ተገልጧል፡- “የምሥራች የምትነግሪ ጽዮን ሆይ፥ ከፍ ወዳለው ተራራ ውጪ፤ የምሥራች የምትነግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ድምፅሽን በኃይል አንሺ፤ አንሺ፥ አትፍሪ፤ ለይሁዳም ከተሞች፡- እነሆ፥ አምላካችሁ! ብለሽ ንገሪ። እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው።’ ኢሳ. 40:9, 10
“የሙሽራውን መምጣት የሚጠባበቁት ‘እነሆ፥ አምላካችሁ!’ ብለው ለሰዎች መናገር አለባቸው። ለዓለም የሚሰበከው የመጨረሻው የምሕረት ብርሃን፣ የመጨረሻው የምሕረት መልእክት የእርሱን የፍቅር ባሕርይ መግለጥ ነው። የእግዚአብሔር ልጆች ክብሩን ሊገልጡ ይገባል። በሕይወታቸው እና በባሕርያቸው የእግዚአብሔር ጸጋ ያደረገላቸውን መግለጥ አለባቸው።
“የጽድቅ ፀሐይ ብርሃን በመልካም ሥራ - በእውነት ቃል እና በቅዱስ ምግባር - ሊያበራ ይገባል።”— ኤለን ጂ. ዋይት፣ የክርስቶስ ምሳሌያዊ ትምህርቶች፣ ገጽ 415, 416
የመወያያ ጥያቄዎች
1. አምላክ የለም ከሚለው አስተሳሰብ የባሰው እግዚአብሔር ይጠላናል የሚለው አስተሳሰብ ነው። ይህ እውነት ቢሆን ኖሮ እኛ የምንኖርበት ዓለም ምን ያህል የተለየ ይሆን ነበር?
2. ዛሬ በዓለማችን የእግዚአብሔርን ባሕርይ በተሳሰተ መንገድ የምንረዳው ለምን ይመስልዎታል? ሰዎች የእግዚአብሔርን ፍቅር በተሻለ መንገድ እንዲመለከቱ ልትረዷቸው የምትችሉባቸውን መንገዶች በማሰብ ተወያዩ።
3. ዛሬ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ሊታወጅ የሚገባው መልእክት ምንድን ነው? የእግዚአብሔርን ፍቅር እውነታ ላልተረዳ ሰው ይህንን መልእክት እንዴት ይገልጹታል? የፍቅሩንና የድንቅ ባሕርይውን እውነታ የሚያሳይ ምን ማስረጃ ሊጠቁሙ ይችላሉ?
4. ስለ እግዚአብሔር ፍቅር መናገር አንድ ነገር ነው። ያንን ፍቅር በሕይወታችን መግለጥ እና ማንፀባረቅ ደግሞ ሌላ ነገር ነው። በዙሪያችን ላሉ የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚያሳዩ “የቅድስና ሥራዎች” ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
Comments
Post a Comment