"የእግዚአብሔር ፍቅር እና ፍትሕ" 3ኛ ትምህርት "እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት "
SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )
ጥር 3 - 9
3ኛ ትምህርት
Jan 11 - 17
እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት
ሰንበት ከሰዓት በኋላ
ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ሉቃ 15፡11–32፣ ሶፎ. 3፡ 17፣ ኤፌ. 5፡25–28፣ ኢሳ. 43፡4፣ ሮሜ. 8፡1፣ ሮሜ. 5:8፣ ማር. 9:17-29።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ አምላክሽ እግዚአብሔር በመካከልሽ ታዳጊ ኃያል ነው፤ በደስታ በአንቺ ደስ ይለዋል፥ በፍቅሩም ያርፋል፥ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል” (ሶፎ. 3፡17)።
እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ ያስቡ፡- የአምስት ዓመት ልጅ በአባቶች ቀን በደንብ ያልተጠቀለለ ስጦታ ይዞ ወደ አባቱ ይመጣል። በደስታ ስጦታውን ለአባቱ ይሰጠዋል። አባትየው “ልጄ፣ ስለ ስጦታህ ግድ የለኝም። እንዲያውም እኔን የሚያስደስት ምንም ነገር ልትሰጠኝ አትችልም። ልትሰጠኝ የምትችለው ሁሉ፣ ራሴ እገዛዋለሁ፣ የምትሰጠኝ ማንኛውም ነገር በገንዘቤ የተገዛ ወይም ከከፈልኩባቸው ቁሳቁሶች የተሰራ ነው። ስለዚህ ስጦታህ ለራስህ ይሁንልህ።
አያስልፈልገኝም። ለማንኛውም ግን እወድሃለሁ” እንዳለው ያስቡ። እህ!
የዚህ አባት ምላሽ ምን ይመስልዎታል? “ጨካኝ”፣ “ቀዝቃዛ” እና “ስሜት- የለሽ” የሚሉት ቃላት ወደ አእምሯችን ይመጣሉ። እግዚአብሔር እንደዚህ ነው ለእኛ ምላሽ የሚሰጠን? በእርግጥ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት እንችላለን? ለመገመት አስቸጋሪ ቢሆንም - የወደቅን፣ በኃጢአት የተጨማለቅን እና ለክፋት የተጋለጥን ብንሆንም እንኳን - አዎን እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት እንችላለን! በሌላ አነጋገር፣ እግዚአብሔር እኛን ወይም የምናመጣቸውን ስጦታዎቻችንን እንደዚያ አባት አይመለከታቸውም። በተቃራኒው፣ በክርስቶስ ብቻ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት እንችላለን። የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት *የሳምንቱን ትምህርት በማጥናት ለሰንበት ይዘጋጁ።
SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )
እሑድ ጥር 4 ,(Jan 12)
ከምትገምተው በላይ ዋጋ ያለው
ቀደም ባለው ትምህርት ላይ እንዳየነው፣ እግዚአብሔር የማይወደው የከፋ ኃጢአተኛ ወይም ክፉ አድራጊ የለም። እግዚአብሔር ለሰዎች ከምንገምተው በላይ ትልቅ ዋጋ ስላለው፣ ስለሚወደንና ኃጢአትም ምን እንደሚያመጣብን ስለሚያውቅ፣ እርሱ የሚያዝነው በኃጢአት ነው።
ሉቃ. 15:11-32ን ያንብቡ። የአባካኙ ልጅ ምሳሌ ስለ እግዚአብሔር ርኅራኄና ፍቅር ምን ያሳየናል? ልክ እንደሌላኛው ልጅ በቤት ላሉ ሰዎች ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል?
ኢየሱስ በተናገረው በዚህ ታሪክ ውስጥ፣ የሰውየው ልጅ አባቱንና የአባቱን ቤተሰብ በመናቅ ርስቱን አስቀድሞ ጠየቀ። አባካኙ ልጅ ድርሻውን ካባከነ በኋላ ደኸየ፤ ተርቦም ከገንዳ በሚመገቡ እርያዎች ቀና። በአባቱ ቤት ያሉ አገልጋዮች ከበቂ በላይ ምግብ እንዳላቸው ሲያስታውስ፣ አገልጋይ ለመሆን ተመኝቶ ወደ ቤቱ ለመመለስ ወሰነ።
ቀጥሎ የሆነው አስገራሚ ነው። አንዳንድ አባቶች እንዲህ ዓይነቱን ልጅ ሲመለስ አይቀበሉትም። “ርስትህን ወስደሃል፣ ከቤቴ ተለይ። ከእንግዲህ እዚህ ቤት የለህም” ይሉታል። ይህ ምክንያታዊ እና ትክክለኛ አስተሳሰብ አይደለም? በአንዳንድ ወላጆች እይታ፣ ልጁ እንደ ልጅ ወደ ቤት ሊቀበሉት ወደ ማይችሉበት ደረጃ ደርሷል።
በምሳሌው ላይ እግዚአብሔርን የሚወክለው አባት ግን በእነዚህ አይነት መንገዶች ምላሽ አይሰጥም። ይልቁንም “እርሱም [አባካኙ ልጅ] ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው” (ሉቃ. 15፡20)።
በዚያን ዘመን አባወራ አንድን ሰው ለመቀበል መሮጥ ነውር ቢሆንም ፣ አባትየው ከታላቅ ርኅራኄው የተነሳ ልጁን ለመገናኘት ሩጦ በጣም በሚያስደንቅ ሁኔታ ወደ ቤተሰቡ ቀላቀለው፤ ግብዣም አደረገለት። ይህ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ለባዘነ ሰው ያለውን ታላቅ ርኅራኄ እና ወደ ቤት ሲመለስም ደስ እንደሚሰኝ የሚያመለክት ነው። እንዴት ያለ የእግዚአብሔር ምስል ነው! የሌላኛው ልጅ ሁኔታ የሚገርም ነው። ለምንድነው ይህ ምላሽ፣ በከፊል ፍትሃዊና ለመረዳት የማያስቸግር፣ የሰው ምላሽ የሆነው? ይሁን እንጂ የሰው ልጅ የፍትሃዊነት ፅንሰ-ሀሳቦች የወንጌልን ጥልቀት ወይም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ሊገልጹት እንደማይችሉ የዚህ ታሪክ ክፍል ምን ያስተምረናል?
SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )
ሰኞ ጥር 5, (Jan 13)
በደስታ ሐሴት ማድረግ
ለመገመት ቢከብደንም፣ እግዚአብሔር እያንዳንዱን ሰው የማይተመን ዋጋ እንዳለው ይቆጥረዋል፤ ለዚህም ነው በአንድ ነፍስ መዳን የሚደሰተው።
ሶፎ. 3:17ን ያንብቡ። ይህ ጥቅስ የአባካኙን ልጅ ምሳሌ ለመረዳት እንዴት ያስችለናል?
ሶፎ. 3፡17 አምላክ በተዋጁት ሕዝቡ ላይ ያለውን ደስታ አጉልቶ ያሳያል።
በዕብራይስጥ ደስታን የሚገልፁባቸው ቃላት ሁሉ በዚህ አንድ ጥቅስ ውስጥ ታጭቀዋል፣ ይህም እግዚአብሔር በተቤዠው ሕዝቡ ደስ እንደሚሰኝ ያሳያል።
በዚያ ቀን የእግዚአብሔርን ደስታ ለመግለጽ ከቃላቶቹ ውስጥ አንዳቸውም ብቻቸውን ብቁ አይሆኑም።
በዚህ ጥቅስ መሠረት እግዚአብሔር በሕዝቡ "መካከል" እንዳለ አስተውሉ። ከፍቅር ግንኙነት የሚመነጨው እርቅ የእግዚአብሔርን መገኘት እውን ያደርጋል። ልክ እንደ አባካኙ ልጅ አባት - ልጁን ከሩቅ ሲያየው እንደሮጠ - እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ነው።
በኢሳ. 62፡4 ላይ ተመሳሳይ መልዕክት ያዘለ የጋብቻ ምሳሌ ይገኛል።
በኢሳ. 62:4 የእግዚአብሔር ሕዝብ “ደስታዬ የሚኖርባት” ተብሎ ሲጠራ፣ ምድሪቱም “ያገባች” ትባላለች። ለምን? ምክንያቱም ጥቅሱ “እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ብሎታልና፥ ምድርሽም ባል ታገባለችና” ይላል። አባቱ በአባካኙ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት ልጅ እንደተደሰተ፣ የእግዚአብሔር የደስታ ጥግ፣ ሕዝቡን በመንግስቱ ተቀብሎ በሚደሰትበት ቀን ይሆናል።
ኤፌ 5:25–28ን ያንብቡ። እኛ እንድናሳይ ስለተጠራንለት የፍቅር ዓይነት ምን ይላል?
ይህ ክፍል ባሎች ሚስቶቻቸውን “ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት እና ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ” እንዲወዷቸው እና “እንደ ገዛ ሥጋቸው” እንዲወዷቸው ይመክራል (ኤፌ. 5፡25፣ 28)። እነዚህ ጥቅሶች ባል ለሚስቱ ሊኖረው ስለሚገባው ከራስ ወዳድነት የጸዳና መስዋዕትነት የሚያስከፍል ፍቅር ብቻ ሳይሆን የሚጠቁሙት፣ ክርስቶስም ራሱ ሕዝቡን (ቤተ-ክርስቲያንን) እንደራሱ እንደሚወዳቸው ያሳያሉ።
SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )
ማክሰኞ ጥር 6, (Jan 14)
እግዚአብሔርን ማስደሰት?
የአለማት ሁሉ አምላክ በዚች ትንሽ ፕላኔት (ዓለም) ውስጥ በሚኖሩ ተራ ሰዎች - ጊዜያዊ የህዋስ ፈሳሽ ነጠብጣቦች - እንዴት ሊደሰት ይችላል? ሁሉን ቻይ ለሆነውና ምንም ለማያስፈልገው ልዑል፣ የሰዎች ጉዳይ ይህን ያህል ግድ የሚለው ለምን ይሆን? እነዚህ ጥያቄዎች በሁለት መልኩ ሊተነተኑ ይችላሉ። በመጀመሪያ እግዚአብሔር ራሱ እንዴት ሊደሰት ይችላል? ሁለተኛ ኃጢአተኛ የሆንን ሰዎች እንዴት ልናስደስተው እንችላለን? የመጀመሪያው ጥያቄ የዛሬው ርዕስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የነገ ይሆናል።
ኢሳ. 43:4ን፣ መዝ. 149:4ን እና ምሳ. 15:8, 9ን ያንብቡ። እግዚአብሔር በሕዝቡ እንዴት ደስ ይለዋል?
ትላንት በከፊል እንዳየነው አምላክ በሰዎች ሊደሰት ይችላል ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰዎችን የሚወዳቸው እንዲሰምርላቸው ነው - ሌሎችን የሚወድና እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት የሚጠነቀቅላቸው እንደሚያደርገው ሁሉ ማለት ነው።
በአንጻሩ ሕዝቡ ክፉ ሲሠሩ እግዚአብሔር ያዝናል። ምሳ. 15:8, 9 የክፉዎች “መሥዋዕት” እና “መንገድ” “በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ” ሲሆን፣ “የቅኖች ጸሎት ግን በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው”፣ ደግሞም “እርሱ ጽድቅን ይወድዳል” በማለት ያስተምራል። ይህ ክፍል እግዚአብሔር በክፋት ማዘኑን፣ በበጎ ነገር ደግሞ መደሰቱን ያሳያል። በተጨማሪም መለኮታዊ ደስታን እና ፍቅርን ጎን ለጎን ያስቀምጣቸዋል፣ ይህም በቃሉ ውስጥ በእግዚአብሔር ፍቅር እና ደስታ መካከል ያለውን ጥልቅ ቁርኝት ያሳያል።
እንደ መዝ. 146፡8 “እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል”። ደግሞም 2 ቆሮ. 9፡7 “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳል” ይላል። በመጀመሪያ እነዚህ ጥቅሶች የማያስተምሩትን አስተውሉ። እግዚአብሔር ጻድቃንን ወይም በደስታ የሚሰጠውን ብቻ ይወዳል አይሉም። እግዚአብሔር ሁሉንም ይወዳል።
ሆኖም እነዚህ ጥቅሶች የሚያስተላልፉት መልዕክት፣ እግዚአብሔር “ጻድቃንን” እና “በደስታ የሚሰጠውን” በተለየ መንገድ ይወዳቸዋል የሚል ነው። በምሳ. 15: 8, 9 ላይ የተመለከትነው ነገር ፍንጭ ይሰጠናል፦ አምላክ ሁሉንም የሚወዳቸው በእነርሱ ደስ በመሰኘት ነው።
የአለማት ፈጣሪ የሆነው አምላክ በስሜት እንኳን ሳይቀር ከእኛ ጋር በመቆራኘቱ፣ ሰማይና ምድር ምን ያህል የተሳሰሩ እንደሆነ ያስቡ።
ይህ አስደናቂ ሐሳብ ምን ተስፋ ሊሰጥዎ ይገባል - በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆኑ?
SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )
ረቡዕ ጥር 7 ( Jan 15)
ሕያዋን ድንጋዮች
የወደቅንና ኃጢአተኛ ፍጡራን ቅዱሱን አምላክ እንዴት ደስ ማሰኘት እንችላለን? ሮሜ 8፡1ን እና ሮሜ 5፡8ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች በእግዚአብሔር ፊት ስላለን ተቀባይነት ምን ያስተምራሉ?
ሰዎች ገና ምላሽ ሳይሰጡ፣ እግዚአብሔር ለሰዎች ጸጋውን ይሰጣቸዋል።
ምንም ሳናደርግ በፊት፣ እግዚአብሔር ወደ እኛ መጥቶ ፍቅሩን እንድንቀበል ወይም እምቢ እንድንል እድሉን ይሰጠናል። ሮሜ 5፡8 “ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል” በማለት ይገልጸዋል (ከኤር. 31፡3 ጋር ያስተያዩ)። እናም አዳኛችን ለኛ በሠራው ሥራ በማመን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ልንታረቅና በፊቱም ደስ ልናሰኘው እንችላለን።
1 ጴጥ. 2:4–6ን አንብበው ከዕብ. 11:6 ጋር ያስተያዩ። እግዚአብሔርን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደምንችል ይህ ምን ይነግረናል?
ያለ እግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት፣ በኃጢአት የወደቁ ሰዎች ምንም ዋጋ ያለው ነገር ለእግዚአብሔር ሊያመጡ አይችሉም። ነገር ግን እግዚአብሔር በጸጋው እና በምህረቱ፣ በክርስቶስ ሥራ መንገድን አዘጋጀ። በተለይም “በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ማቅረብ” እንችላለን (1ጴጥ. 2፡5)። ምንም እንኳን “ያለ እምነት እርሱን ደስ ማሰኘት ባይቻልም” (ዕብ. 11፡6)፣ በክርስቶስ የማስታረቅ ሥራ፣ እግዚአብሔር “በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ፥ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን” ይላል (ዕብ. 13:21)። የርሱ ጽድቅ ብቻ ተቀባይነት ስላለው፣ በክርስቶስ ምልጃ ለእግዚአብሔር በእምነት ምላሽ የሚሰጡ፣ በእርሱ ፊት ጻድቃን ሆነው ይቆጠራሉ። ለእግዚአብሔር ፍቅር ምላሽ የሚሰጡ በክርስቶስ ምልጃ ምክንያት ብቁ ሆነው ይቆጠራሉ (ሉቃ. 20፡35)፤ እርሱም እርሱን እንዲመስሉ ይለውጣቸዋል (1ቆሮ. 15፡51-57፣ 1ዮሐ. 3፡2)። የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ለእኛ ብቻ የሚደረግ ሳይሆን፣ በእኛ ውስጥም የሚፈፀም ነው።
ክርስቶስ በሰማይ ስለ እናንተ የሚማልድ መሆኑ የሚያበረታታ የሆነው ለምንድን ነው? እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት
SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )
ሐሙስ ጥር 8 (Jan 16)
የከበረ አላማ
በእግዚአብሔር ምሕረትና ምልጃ ጥላ ስር፣ ለፍቅሩ ትንሽዬ አዎንታዊ ምላሽ እንኳን ስንሰጥ እግዚአብሔር ደስ ይለዋል። ብቻውን ሊወደድ በሚገባው እና ፍጹም ጻድቅ በሆነው በርሱ በኩል፣ እያንዳንዳችን ጻድቃን ተብለን፣ በእግዚአብሔር ተወደው ለዘላለምም ከርሱ ጋር ፍጹም በሆነ ፍቅር ከሚኖሩት ጋር ልንቆጠር እንችላለን። ይህ ታላቅ የመቤዠት ተስፋ ነው፣ እሱም ክርስቶስ በሰማይ ለእኛ የሚሰራውን ሥራ ያካትታል።
ግን ይህ እኔንም ሊያካትት ይችላል? ብለው ሊደነቁ ይችላሉ። ብቁ ባልሆንስ? በቂ እምነት የለኝም ብዬ ብፈራስ? ማር. 9:17-29ን ያንብቡ። ክርስቶስ በታሪኩ ውስጥ ላለው ሰው ምን ምላሽ ሰጠው? ምን ያህል እምነት ነው በቂ እምነት ሊሆን የሚችለው?
ደቀ መዛሙርቱ ጋኔኑን ማውጣት አልቻሉም፤ ተስፋው ሁሉ የተሟጠጠ መሰለ። ኢየሱስ ግን ቀርቦ ለአባቱ ‘‘ብታምን፣ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል’’ አለው (ማር. 9፡23)። አባትየውም በእንባ፡- "ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው አለ” (ማር. 9፡24)።
ኢየሱስ ሰውየውን፣ “እምነት ሲኖርህ ወደ እኔ ተመለስ” እንዳላለው አስተውሉ። ይልቁንም “አለማመኔን እርዳው” የሚለው ጩኸቱ በቂ ነበር።
ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም (ዕብ. 11፡6)፤ ሆኖም ኢየሱስ ትንሿን እምነት እንኳን ይቀበላል። እናም በእምነት (በክርስቶስ የምልጃ ሥራ) እርሱን ደስ ማሰኘት እንችላለን። በእምነት እና ክርስቶስ በእኛ ፈንታ ባደረገው ሥራ፣ አምላክን በሚያስደስት መንገድ ምላሽ መስጠት እንችላለን - ምድራዊ አባት ልጁ ብዙም ዋጋ የሌለው ስጦታ ሲያመጣለት እንደሚደሰት ሁሉ ማለት ነው። የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
ስለዚህ የጳውሎስን ምክር በመከተል እግዚአብሔርን ‘ማስደሰት’ አላማችን ሊሆን ይገባል (2 ቆሮ. 5:9, 10፤ ከቆላ. 1:10፣ 1 ተሰ. 4:1፣ ዕብ. 11፡5 ጋር ያስተያዩ)። እናም የምንወዳቸውን ሰዎች ፍላጎት ለመሙላት የኛን ምኞት እንዲለውጥልን እና ፍቅራችን ለሌሎች እንዲደርስ እንዲያሰፋው እግዚአብሔርን ልንጠይቀው ይገባል። “በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጸኑ፤ ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ለመቀበል ትጉ” (ሮሜ. 12፡10–13፣)።
እግዚአብሔር በክርስቶስ የሚቀበለን ከሆነ፣ እኛስ ሌሎችን እንዴት አብልጠን መቀበል አለብን? ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚለው ትእዛዝ (ዘሌ. 19፡18፣ ማቴ. 22፡39) እና ሰዎች ሊያደርጉልህ የምትፈልገውን አንተም እንዲሁ አድርግላቸው የሚለው ወርቃማው ሕግ ይህን ሃሳብ እንዴት ይገልጹታል?

Comments
Post a Comment