"እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ"
"እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤" 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡27 ታናሾችን የሚመርጥ ጌታ ነው ያለን! ታናሾችን መምረጡ ደግሞ ከታላቅነቱ ጋር ተጋጭቶበት አያውቅም። ሚዛኑ ከዓለም ሚዛን በእጅጉ ይለያል። ጌታ ሲመርጥ አያወሳስብም፤ የጌታ መስፈርት ቅንነት፣ ተቀባይነት(ክፍት ልብ)፣ ምልስነት እና ትሁትነት ነው። እነዚህ ባህሪዎች ደግሞ በገንዘብ ብዛት፣ በሥልጣን እርከን፣ የንጉሳዊያን ቤተሰብ በመሆንና በዕውቀት ብዛት የሚመጡ አይደሉም። ወዶ ለተቀበላቸው ሁሉ በምድር ላለው 8 ቢሊየን ህዝብ ሁሉ በነፃ የቀረቡ የባህሪ ምርቶች ናቸው። እንኳን ደስ ያለህ ወንድሜ! እንኳን ደስ አለሽ እህቴ! መላዕክት ያለ ምንም ህፀፅ እና ነቁጥ ሆነው የሚያገለግሉት ይህ ጌታ እነዚህን ባህሪያት በመውረስ ያለ ምንም ከባድ መስፈርት ታገለግሉት ዘንድ መርጧችኋል። በደካሞቹ ለመገልገል መርጧል። ልብ ላለው(ሲጠብቅም ሲላላም) ይህ ክቡር ዕድል ነው! እነሆ ይህንን ከመረዳት የተነሳ “የሚያገለግል ሰው ጠፋ!” የሚለው ድምፅ ከቤተክርስቲያን እንዲጠፋ እንጸልይ። ሁሉም ሰው፣ ይህንን ክቡር ጌታ ለማገልገል የሚሽቀዳደምበትን ዘመን ያምጣልን። መልካም ቀን! ጥር 2፣ 2017 ዓ.ም




Comments
Post a Comment