"የእግዚአብሔር ፍቅር እና ፍትሕ" 2ኛ ትምህርት " ኪዳናዊ ፍቅር"

 

                                              SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )

                                                         ታህሣሥ 26 - ጥር 2

                                                                 2ኛ ትምህርት

                                                                       Jan 4 - 10

                                                             ኪዳናዊ ፍቅር

                                                      ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- 2ጴጥ. 3:9፣ ዘዳ. 7፡6–9፣ ሮሜ. 11:22፣ 1 ዮሐ. 4:7-20፣ ዮሐ. 15:12፣ 1 ዮሐ. 3:16


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ ኢየሱስም መለሰ አለውም:- የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፣ ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን” ( ዮሐንስ 14፡23)። 


         አጋፔ የሚለው የግሪክ ቃል ልዩ የሆነውን የእግዚአብሔርን ፍቅር እንደሚያመለክት፣ እንደ ፊልዮ ያሉት ሌሎች የፍቅር ቃላት ደግሞ ከአጋፔ ያነሱ የተለያዩ የፍቅር ዓይነቶችን እንደሚያመለክቱ ብዙዎች ተምረዋል። አንዳንዶች አጋፔ የአንድ ወገን ፍቅርን፣ የሚሰጥ ብቻ እንጂ የማይቀበል፣ በሰው ምላሽ የማይወሰን ፍቅርን ያመለክታል ይላሉ። 

           ሆኖም በቃሉ ያለውን መለኮታዊ ፍቅር በጥንቃቄ ስናጠና፣ እነዚህ አመለካከቶች ምንም እንኳን በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ቢሆኑም የተሳሳቱ መሆናቸውን ያሳያል። በመጀመሪያ፣ አጋፔ የሚለው የግሪክ ቃል የእግዚአብሔርን ፍቅር ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ፍቅርን፣ አንዳንድ ጊዜ የተሳሳተ የሰው ፍቅርን ጭምር ያመለክታል (2ጢሞ. 4፡10)። ሁለተኛ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከአጋፔ በተጨማሪ ሌላ ብዙ ቃላት የእግዚአብሔርን ፍቅር ያመለክታሉ። 

ለምሳሌ፣ ኢየሱስ ሲያስተምር “እናንት ስለወደዳችሁኝ [ፊሊዮ]፣ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋል [ፊሊዮ]” ይላል (ዮሐንስ 16፡27)። እዚህ ላይ ፊሌዮ የሚለው የግሪክ ቃል የሰውን ፍቅር ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅርም ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል። ስለዚህ ፊልዮ ጎደሎ የሆነውን የፍቅር ዓይነት ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርንም ፍቅር ያመለክታል። ኪዳናዊ ፍቅር 

በተጨማሪ ቅዱሳት መጻህፍት የእግዚአብሔር ፍቅር የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ጥልቅ ግንኙነትን የሚጠይቅ እንደሆነ፣ ፍቅሩንም ለእርሱ እና ለሌሎች መልሰው ማንጸባረቅ ወይም አለማንፀባረቃቸው ለእግዚአብሔር ትልቅ ልዩነት እንዳለው ያስተምራሉ።


                                           SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )

                                                               እሑድ

                                                           ታህሣሥ 27, (Jan 5)

                                                  ዘላለማዊው የእግዚአብሔር ፍቅር

              ቃሉ ግልጽ ነው፡- እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው ይወዳል። በጣም የታወቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ዮሐንስ 3፡16 ይህንን እውነት ያውጃል፡ - “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” መዝ. 33:5 እና መዝ. 145:9ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ እግዚአብሔር ፍቅር፣ ርኅራኄና ምሕረት ስፋት ምን ያስተምራሉ?

              አንዳንዶች የማይወደዱ እንደሆኑ ሊሰማቸው ይችላል፣ ወይም ከነሱ በቀር እግዚአብሔር ሌላውን ሁሉ ይወዳል ብለው ያስቡ ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሔር የተወደደ እንደሆነ ይናገራል።   እርሱ የማይወደው ማንም የለም። እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው ስለሚወድ፣ ሁሉም እንዲድኑ ይፈልጋል።   2 ጴጥ. 3:9ን፣ 1 ጢሞ. 2:4ን እና ሕዝ. 33:11ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው ለማዳን ስላለው ፍላጎት ምን ያስተምራሉ?

                ከዮሐ. 3፡16 በኋላ ያለው ጥቅስ፡- “ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፣ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና” ይላል (ዮሐ. 3፡ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት 17)። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ (ፍላጎት) ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሁሉም ሰው ፍቅሩን ተቀብሎ ይድን ነበር። ሆኖም ጌታ ፍቅሩን እንዲቀበሉ ማንንም አያስገድድም።   ሰዎች ሊቀበሉት ወይም ሊንቁት መብት አላቸው።   ምንም እንኳን አንዳንዶች ባይቀበሉትም፣ እግዚአብሔር እነርሱን መውደድ አያቆምም። በኤር. 31፡3 ላይ ለሕዝቡ፡- “በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ ስለዚህ በቸርነት ሳብሁሽ” ይላል። መጽሐፍ ቅዱስ በሌላ ስፍራ ደጋግሞ እንደሚያስተምረው የእግዚአብሔር ፍቅር ለዘላለም ይኖራል (ለምሳሌ መዝ. 136ን ይመልከቱ)። የእግዚአብሔር ፍቅር በጭራሽ አያልቅም። ዘላለማዊ ነው። ብዙ ጊዜ ሌሎችን አለመውደድ ስለሚቀልለን፣ ይህን እውነት መረዳት ይከብደናል፤ አይደለም እንዴ?   ነገር ግን፣ እኛ በግላችን የዚህን ፍቅር እውነታ ብንለማመደው— የእግዚአብሔርን ፍቅር በግላችን ብናውቀው —እንዴት ያለ የተለየ ህይዎት በኖርንና ሌሎችንም በተንከባከብን ነበር ።   እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው የሚወድ ከሆነ፣ ይህ ማለት አስጸያፊ ባሕርይ ያላቸውንም ይወዳል ማለት ነው። አምላክ ለእነዚህ ሰዎች ያለው ፍቅር እኛ ከእነርሱ ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት ምን ሊያስተምረን ይገባል? 

                                           SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )

                                                                     ሰኞ

                                                        ታህሣሥ ( 28Jan 6)

                                          ኪዳናዊ ፍቅር

                       መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ያለውን የተለየ የፍቅር ግንኙነት የሚገልጸው፣ በቤተሰብ ወይም በዝምድና በተለይም በባልና በሚስት ወይም መልካም እናት ለልጇ ያላትን ፍቅር የሚያሳዩ ዘይቤዎችን በመጠቀም ነው። እነዚህ ዘይቤዎች በተለይ በእግዚአብሔር እና በቃል ኪዳኑ ህዝቦች መካከል ያለውን የተለየ ግንኙነት ለማሳየት ያገለግላሉ። ይህ ግንኙነት ኪዳናዊ ፍቅር ነው፡- ይህም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎች ይህን ፍቅር ተቀብለው በምላሹ እርሱን እና አንዱ ሌላውን እንዲወድ ይጠብቃል። ኪዳናዊ ፍቅር ዘዳ. 7:6–9ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን እና በእግዚአብሔር ፍቅር መካከል ስላለው ግንኙነት ምን ያስተምራሉ?

                 ዘዳ. 7፡9 እግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ ሕዝብ ያለውን የተለየ ፍቅር ይገልጻል፣ ግንኙነቱ በከፊል ታማኝ በመሆናቸው ወይም ባለመሆናቸው ላይ የተመሰረተ ነው። የእግዚአብሔር ፍቅር በሁኔታዎች የተመሰረተ አይደለም፣ ነገር ግን ከሕዝቡ ጋር ያለው የቃል ኪዳን ግንኙነት በሁኔታዎች የተመሰረተ ነው።   በዘዳ. 7፡9 ላይ “ርኅራኄ” ወይም “ምሕረት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ኼሴድ ራሱ የመለኮታዊ ፍቅርን ኪዳናዊ ገጽታ ያሳያል። ኼሴድ ብዙ ጊዜ ታላቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ምሕረት፣ መልካምነትና ፍቅር ለመግለጽ ጥቅም ላይ ውሏል። በተለይ ኼሴድ በፍቅር ግንኙነት ውስጥ አንዱ ለሌላው ወገን ያለውን ጽኑ ፍቅር ያመለክታል። ሌላውም ወገን በምላሹ ይህን ፍቅር እንዲያሳይ ግንኙነቱ ያነሳሳዋል።   የእግዚአብሔር ኼሴድ ፍቅሩ እጅግ አስተማማኝ፣ ጽኑ እና ዘላለማዊ እንደሆነ ያሳያል። ሆኖም የኼሴድን በረከቶች መቀበል በሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ነው፡- ሕዝቡ ለመታዘዝ እና ቃላቸውን ለመጠበቅ ባላቸው ፈቃደኝነት ማለት ነው (2 ሳሙ. 22:26፣ 1 ነገ. 8:23፣ መዝ. 25:10፣ መዝ. 32:10፣ 2 ዜና 6:14)።   የእግዚአብሔር ጽኑ ፍቅር የሁሉም የፍቅር ግንኙነቶች መሠረት ነው፣ ያንን ፍቅርም በፍጹም ልንደርስበት አንችልም። እግዚአብሔር በሕይወት እንድንኖር ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ ስለ እኛ ራሱን በፈቃዱ ሰጠ። "ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም" (ዮሐ. 15:13)። ትልቁ የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠው ጌታ “ራሱን አዋርዶ፣ ለሞት ይኸውም ለመስቀል ሞት እንኳ በታዘዘ ጊዜ” (ፊልጵ. 2፡8) እንደሆነ ምንም አያጠያይቅም።   የእግዚአብሔርን ፍቅር እውነታ በሃሳብህ ውስጥ ያለማቋረጥ ማሰላሰል የምትችልባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? ይህን ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?


                                 SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )

                                                  ማክሰኞ

                                            ታህሣሥ 29    ,( Jan 7)

                                             በሁኔታዎች የተመሠረተ ግንኙነት

                          እግዚአብሔር እያንዳንዱን ሰው ከእርሱ ጋር የጠበቀ የፍቅር ግንኙነት እንዲኖረው ይጋብዛል (ማቴ. 22፡1–14ን ይመልከቱ)። ለዚህ ጥሪ ተገቢውን ምላሽ መስጠት እግዚአብሔርን እና ሌሎችን እንድንወድ የተሰጠንን ትዕዛዝ መታዘዝን ያካትታል (ማቴ. 22፡37–39ን ይመልከቱ)። አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን የቃል ኪዳኑን በረከቶች የሚያገኘው ይህንን ፍቅር ለመቀበል ወይም ላለመቀበል በሚያደርገው ውሳኔ ነው።   ሆሴ. 9:15ን፣ ኤር. 16:5ን፣ ሮሜ 11:22ን እና ይሁ. 21ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ከእግዚአብሔር ፍቅር የተነሳ የምናገኛቸውን በረከቶች ልናጣቸው እንደምንችል ምን ያስተምሩናል?

                       በእነዚህ እና በሌሎች ጥቅሶች ተደጋግሞ እንደተገለፀው፣ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን የፍቅር ግንኙነት በረከቶቹን የምንለማመዳቸው ለፍቅሩ ምላሽ ስንሰጥ ብቻ ነው። ሆኖም አምላክ ሰውን መውደዱን ያቆማል ብለን በማሰብ ልንሳሳት አይገባም። እንዳየነው የእግዚአብሔር ፍቅር ዘላለማዊ ነው። ምንም እንኳን ሆሴዕ 9፡15 ላይ እግዚአብሔር ስለ ሕዝቡ ሲናገር፡- “ከእንግዲህ ወዲያ አልወድዳቸውም’’ ቢልም፣ በኋላ ላይ በዚያው መጽሐፍ እግዚአብሔር ስለ ሕዝቡ “በፈቃዴ እወድዳቸዋለሁ’’ ብሎ እንደተናገረ ማስታወስ አስፈላጊ ነው (ሆሴ. 14:4)። ሆሴ. 9፡15 እግዚአብሔር ሕዝቡን መውደድ አቁሟል አይልም።   ይልቁንም ከእግዚአብሔር ጋር ያለን የፍቅር ግንኙነት በረከት በሁኔታዎች ላይ የተመረኮዘ መሆኑን እያመለከተ ነው። ይህም ግንኙነት እንዲቀጥል ለፍቅሩ የምንሰጠው ምላሽ ወሳኝ ነው።   "ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ” (ዮሐ. 14:21)። በተመሳሳይ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ፡- “እናንተ ስለወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋል” ብሏቸዋል (ዮሐንስ 16፡27)።   እነዚህ እና ሌሎች ጥቅሶች የሚያስተምሩን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ኪዳናዊ ፍቅር በሚኖረን የሚያድን ግንኙነት ምክንያት የምናገኛቸውን በረከቶች ማስቀጠል የምንችለው የእግዚአብሔርን ፍቅር ለመቀበል ፈቃደኛ ስንሆን ነው። ይህ ደግሞ ፍቅሩን ለሌሎች ለማድረስ የሚገለገልብን ዕቃዎች መሆንን ይጨምራል። ይህ ማለት ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በምንም ሁኔታ ያቆማል ማለት አይደለም።   ይልቅስ ፀሐይን እንዳታበራ ማድረግ እንደማንችል፣ ከጨረሮቿ ግን ራሳችንን መሰወር እንደምንችል ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ፍቅር ለማቆም ምንም ነገር ማድረግ አንችልም፤ ሆኖም ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ችላ ብለን የሚሰጠንን በረከት በተለይም የዘላለም ሕይወት ተስፋ ልናጣ እንችላለን።   ሰዎች ምላሽ ቢሰጡም ባይሰጡም፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር እውነታ የሚያዩባቸው እና የሚለማመዱባቸው መንገዶች ምንድናቸው? ለምሳሌ፣ ከኃጢአት ውድቀት በኋላ እንኳን ተፈጥሮ ፍቅሩን እንዴት ይገልጣል? 

                                           SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )

                                                            ረቡዕ

                                                ታህሣሥ 30, (Jan 8)

                                          ችላ የተባለው ምሕረት

                የእግዚአብሔር ፍቅር ዘላለማዊ እና ምንጊዜም ሳይገባን የተሰጠን ነው።ይሁን እንጂ ሰዎች ላይቀበሉት ይችላሉ። ምንም ሳናደርግ ፍጹምና ዘላለማዊ በሆነው ፍቅሩ አስቀድሞ እንዲሁ ስለወደደን ብቻ (ኤር. 31፡3)፣ ይህን ፍቅር ለመቀበልም ሆነ ችላ ለማለት እድሉ አለን። ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር፣ አስቀድሞ ሳንጠይቅ ለተሰጠን ፍቅር ምላሽ ነው።

1 ዮሐ. 4:7–20ን በተለይ ቁጥር 7 እና 19 ያንብቡ። ይህ ጥቅስ የእግዚአብሔር ፍቅር ቅድሚያ ስለሚሰጠው ነገር ምን ይነግረናል?

                  ሁልጊዜ የሚቀድመው የእግዚአብሔር ፍቅር ነው። እግዚአብሔር አስቀድሞ ባይወደን፣ መልሰን ልንወደው አንችልም ነበር። እግዚአብሔር ለመውደድም ሆነ ልንወደድ የምንችል አድርጎ ቢፈጥረንም፣ የፍቅር ሁሉ መሰረቱና ምንጩ ግን እግዚአብሔር ራሱ ነው። ሆኖም ልንቀበለውና በሕይወታችን ልናንጸባርቀው ምርጫ አለን። ይህ እውነት ክርስቶስ በተናገረው ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ባልሆነው አገልጋይ ምሳሌ ተገልጿል (ማቴ. 18፡23–35ን ይመልከቱ)። የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት 

              በምሳሌው ላይ አገልጋዩ የጌታውን ዕዳ የሚከፍልበት ምንም አይነት መንገድ እንዳልነበረ እናያለን። እንደ ማቴ. 18 አገልጋዩ ከጌታው የ10,000 መክሊት ዕዳ ነበረበት። አንድ መክሊት 6,000 ዲናር የሚያህል ነበር። አንድ ዲናር ደግሞ ለአንድ ተራ ሠራተኛ ለቀን ሥራ የሚከፈለው ነበር (ከማቴ. 20፡2 ጋር ያነፃፅሩ)። 

               ስለዚህ አንድ መክሊት ለማግኘት አንድ ተራ ሰራተኛ ለ6,000 ቀናት የጉልበት ሥራ ይሰራል። የዕረፍት ቀናትን ሳይጨምር አንድ ተራ ሠራተኛ በዓመት 300 ቀናትን በመሥራት በዓመት 300 ዲናር ሊያገኝ ይችላል እንበል። ስለዚህ አንድ መክሊት ዕዳ ለመክፈል አንድ ተራ ሰራተኛ 20 ዓመት ገደማ ይፈጅበታል (6,000 ዲናር ÷ 300 = 20)። 10,000 መክሊት ለማግኘት አንድ ተራ ሠራተኛ በአማካይ 200,000 ዓመታት መሥራት ይኖርበታል። ባጭሩ አገልጋዩ ይህንን ዕዳ ፈጽሞ ሊከፍል አይችልም ነበር። ሆኖም ጌታው ለአገልጋዩ ስለ ራራለት ያለበትን ትልቅ ዕዳ እንዲሁ ተወለት። 

            ይህ ምሕረት የተደረገለት አገልጋይ፣ ትንሿን የ100 ዲናር ዕዳ ለባልንጀራው ባለመተው ወደ እስር ቤት ሲያስገባው፣ ጌታው ተቆጥቶ ይቅርታውን አነሳ። 

         አገልጋዩ የጌታውን ፍቅርና ይቅርታ አጣ። ምንም እንኳን የእግዚአብሔር ርኅራኄ እና ምሕረት የማያልቁ ቢሆንም፣ ሰው በስተመጨረሻ በረከቶቹን ሊገፋቸው፣ እንዲያውም ሊያጣቸው ይችላል። 


             ይቅር የተባልከውን እና በኢየሱስ ይቅር ለመባል ምን ዋጋ እንደከፈልክ አስብ። ሌሎችን ይቅር ስለማለት ይህ ምን ሊነግርህ ይገባል? 

                                        SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )

                                                                   ሐሙስ

                                                                    ጥር 1 , (Jan 9)

                                                በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ

                አገልጋዩ የጌታውን ዕዳ በጭራሽ መክፈል እንደማይችል ሁሉ፣ እኛም ለእግዚአብሔር ምንም ልንከፍለው አንችልም። የእግዚአብሔርን ፍቅር በሥራችን ልናገኘው አንችልም። “ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል” (ሮሜ. 5፡8)። እንዴት ያለ አስደናቂ ፍቅር ነው! 1ኛ ዮሐ. 3፡1 “የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ” ይላል።   ልናደርግ የምንችለው እና ማድረግ ያለብን የአምላክን ፍቅር ለሌሎች ኪዳናዊ ፍቅር ማሳየት ነው። እንዲህ ያለ ታላቅ ርኅራኄ እና ይቅርታ ከተቀበልን፣ እንዴት አብልጠን ለሌሎች ልንራራ እና ይቅርታ ልናደርግ ይገባናል? አገልጋዩ ለባልንጀራው አገልጋይ ምሕረት ስላላደረገለት፣ የጌታውን ርኅራኄና ይቅርታ ማጣቱን አስታውሱ። እግዚአብሔርን በእውነት የምንወደው ከሆነ፣ ፍቅሩን ለሌሎች ከማሳየት ወደ ኋላ አንልም።   ዮሐ. 15:12ን፣ 1 ዮሐ. 3:16ን፣ እና 1 ዮሐ. 4:7–12ን ያንብቡ። እነዚህ ክፍሎች በእግዚአብሔር ፍቅር እና እኛ ለርሱ እና ለሌሎች ባለን ፍቅር መካከል ስላለው ግንኙነት ምን ያስተምሩናል?

             ከዮሐ. 15፡12 በኋላ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ "እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ" ብሏቸዋል (ዮሐ 15፡14)። ኢየሱስ ምን አዟቸው ነበር? እርሱ እንደወደዳቸው ሌሎችን እንዲወዱ አዟቸው ነበር። ጌታ እዚህ እና ሌሎች ክፍሎች ላይ፣ እግዚአብሔርን እንድንወድ እና እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ያዘናል።   ባጭሩ ልንገነዘበው የሚገባን ልንቆጥረው እና ፈጽሞ ልንከፍለው የማንችለው ዕዳ ይቅር ተብሎልናል። ይህም የሆነው በመስቀሉ ብቻ ነው።   ስለዚህ እግዚአብሔርን ልንወደውና ልናመሰግነው፣ ከሌሎችም ጋር በፍቅር እና በጸጋ ልንኖር ይገባናል። ሉቃ. 7፡47 እንደሚያስተምረን ብዙ ይቅር የተባለለት ብዙ ይወዳል፣ ነገር ግን “ጥቂት የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል።” ከመካከላችን ምን ያህል ይቅር እንደተባለ የማያስተውል ማን አለ?   እግዚአብሔርን መውደድ ሌሎችን መውደድን የሚያካትት ከሆነ፣ በቃልም ሆነ በድርጊት የእግዚአብሔርን የፍቅር መልእክት በአስቸኳይ ልናካፍል ይገባል። አሁኑኑ ሰዎችን በዕየለት ኑሯቸው መርዳት አለብን፤ የእግዚአብሔር ፍቅር ቧንቧ በመሆን ሰዎችን በአዲስ ሰማይ እና በአዲስ ምድር የዘላለም ሕይወት ተስፋን ወደሚሰጣቸው ወደ እርሱ ልናመለክታቸው ይገባል - የእግዚአብሔርን ፍቅር እንቢ በማለት ከዚህ በኃጢአትና በሞት ፍሬ ከተበላሸው ዓለም ፍጹም የተለየ አዲስ ፍጥረት። የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት ሌሎችን በመውደድ እግዚአብሔርን ለመውደድ ምን የተለየ እርምጃ መውሰድ ይችላሉ? ዛሬና በሚቀጥሉት ቀናት ለሰዎች የእግዚአብሔርን ፍቅር ለማሳየትና የዘላለምን ሕይወት ተስፋ እነዲያጣጥሙ ለመጋበዝ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? 

                                                        SABBATH SCHOOL(ሰንበት ትምህርት )

                                                                   ዓርብ

                                                              ጥር 2 (Jan 10)

                                                            ተጨማሪ ሀሳብ

                          ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ መንገድ ከሚለው የኤለን ጂ. ኋይት መጽሐፍ “የፀሎት እድል” የተሰኘውን ርዕስ ከገጽ 93–104 ያንብቡ።   “ፍላጎቶቻችሁን፣ ደስታችሁን፣ ሀዘኖቻችሁን፣ ጭንቀታችሁን እና ፍርሃቶቻችሁን በእግዚአብሔር ፊት አስቀምጡአቸው። እርሱን ሸክም አታበዙበትም፣ አታደክሙትምም። የራሳችሁን ፀጉር የሚቆጥረው ለልጆቹ ፍላጎት ደንታ ቢስ አይደለም። ‘ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና’ (ያዕ 5፡ 11)። የፍቅር ልቡ በሀዘናችን እና ሀዘናችንን በመናገራችን ይነካል። አእምሯችሁን ግራ የሚያጋባውን ነገር ሁሉ ወደ እርሱ ውሰዱት። ዓለማትን በእጁ ለያዘው እና ሁሉንም ጉዳዮች ለሚቆጣጠረው ለእርሱ፣ ሊሸከመው የማይችለው ምንም ነገር የለም። በምንም መልኩ ሰላማችንን የሚያውክ ማንኛውም ነገር፣ እርሱ የማያስተውለው ትንሽ ነገር አይደለም። በእኛ ተሞክሮ ውስጥ እርሱ የማያነበው ድቅድቅ ጨለማ የሆነ ምዕራፍ የለም፤ ሊፈታው የሚከብደው ግራ መጋባት የለም። የሰማዩ አባታችን የማይመለከተው ወይም ወዲያውኑ ፍላጎት የማያድርበት ከታታናሾቹ ባንዱ ላይ የሚመጣ ጥፋት፣ ነፍሳችንን የሚከብ ጭንቀት፣ የሚያበረታን ደስታ፣ ከከናፍራችን የሚወጣ ልባዊ ጸሎት አይኖርም።   ‘ልባቸው የተሰበረውን ይፈውሳል፤ ቁስላቸውንም ይጠግናል’ (መዝ. 147፡3)። በምድር ላይ የእርሱን ጥንቃቄ የሚጋራ እና የሚወደውን ልጁን የሰጣት ሌላ ነፍስ የሌለች እስኪመስል ድረስ፣ በእግዚአብሔር እና በእያንዳንዱ ነፍስ መካከል ያለው ግንኙነት የተለየ እና ሙሉ ነው።”—ኤለን ጂ. ዋይት፣ ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ መንገድ፣ ገጽ 100. ኪዳናዊ ፍቅር   

                                            የመወያያ ጥያቄዎች

 1. “በምድር ላይ የእርሱን ጥንቃቄ የሚጋራ እና የሚወደውን ልጁን የሰጣት ሌላ ነፍስ የሌለች እስኪመስል ድረስ፣ በእግዚአብሔር እና በእያንዳንዱ ነፍስ መካከል ያለው ግንኙነት የተለየ እና ሙሉ ነው” የሚለውን ከላይ ያለውን ዓረፍተ ነገር ያሰላስሉ። ይህ ምን አይነት መጽናናትን ይሰጥዎታል? እግዚአብሔር ለርሶ ቅርብ እና የሚጠነቀቅልዎት መሆኑን በማወቅ ሕይወትዎን እንዴት መኖር አለብዎት? በዚህ አስደናቂ ተስፋ መኖርን እንዴት መማር ይችላሉ? በየዕለቱ ይህን በእውነት በማመን ብኖረው ብለው ያስቡ። 

  2. ከዚህ ሳምንት ትምህርት አንጻር መዝ. 103:17, 18ን እንዴት ይረዱታል? የእግዚአብሔር ፍቅር ዘላለማዊ ቢሆንም ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት የሚያስገኛቸው በረከቶች ፍቅሩን በመቀበላችን ላይ መመርኮዙን እንዴት ያሳያል? 

  3. ይህን ማወቅዎ ከአምላክ ጋር ባለዎት ግንኙነት ላይ ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው? የሌሎችን ሀዘን የሚያስቡበትን መንገድ እንዴት ይቀይረዋል?



Comments

Popular posts from this blog

"እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ"

"ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች"/ Night is coming, when no one can work."/

"የእግዚአብሔር ፍቅር እና ፍትሕ" 1ኛ ትምህርት "እግዚአብሔር እንዲሁ ይወዳል::"